መረጃን የምንገበይበት መንገድ ይቀየር
መረጃን የምንገበይበት መንገድ ይቀየር
በአሁኑ ዘመን እውቀት፣ አመለካከትና ክህሎታችንን የምንገነባው በምንጠቀማቸው የመረጃ ምንጮች ልክ ነው። ከአሉባልታ፣ ከሰፈር ወሬና "በሬ ወለደ" መረጃዎችን ከመሰብሰብ ወጥተን ወደ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የመረጃ መረቦች መዞር የግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን።
ዛሬ ላይ እውቀትን ለማግኘት የታተሙ መጽሐፍትን ብቻ መጠበቅ አዋጭ ላይሆን ይችላል፤ ዲጂታል አማራጮች ወጪን በመቀነስና ፍጥነትን በመጨመር ረገድ ቀዳሚ ናቸው። በተለይም እንደ AI (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እጅግ ውጤታማ የመረጃ ምንጮችና የሥራ መሣሪያዎች ናቸው።
AI መሣሪያ (Tool) እንጂ ተዓምር አይደለም!
አንድ አካፋ አፈር የሚያፍሰው በራሱ ሳይሆን እኛ በእጃችን ይዘን ስንጠቀምበት ነው። AI-ም እንዲሁ መረጃን በቀላሉ የምናገኝበት "ዘመናዊ አካፋ" (መሣሪያ) እንጂ የሰው ልጅ አእምሮ ምትክ አይደለም። ከእሱ የምናገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የሚከተሉትን ነጥቦች ማስተዋል ይኖርብናል፦
1. Prompt Engineering፦ ከAI ጋር እንዴት መግባባት እንዳለብን ማወቅና መሠልጠን ይኖርብናል። በትክክል ስንጠይቅ በትክክል እንረዳለን።
2. ማረጋገጥና ማሰላሰል፦ AI ሁልጊዜ ትክክል ነው ማለት አይደለም። መረጃዎችን ወስዶ ማሰብ፣ ማሰላሰልና እንደ Google ባሉ መፈለጊያ መረቦች ላይ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
3. የመረጃው ዓይነት፦ AI እንደ ሳይንስ፣ ሒሳብና ፕሮግራሚንግ ባሉ ዘርፎች ላይ ስህተት የመሥራት ዕድሉ እጅግ አናሳ ነው። በተቃራኒው ግን በታሪክ፣ በሃይማኖትና መሰል ጉዳዮች ላይ ስህተት የመሥራት ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
የወደፊቱ የሥራ ዓለምና AI
ወደ ፊት AI ሰዎችን በቀጥታ ከመተካት ይልቅ፣ AIን መጠቀም የሚችሉ ብቃት ያላቸው ሰዎች AIን መጠቀም የማይችሉትን በመተካት የሥራ ገበያውን ሊቆጣጠሩት ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት በሰለጠነው ዓለም ትላልቅ ባንኮች፣ የጦር መሣሪያዎች፣ አውሮፕላኖችና መኪኖች፣ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሆቴሎች ከAI ጋር በመተሳሰር እጅግ አስተማማኝና ቀልጣፋ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ።
ባጭሩ፣ AI-ን እንደ ምርጥ ረዳት መሣሪያ እንጠቀምበት፤ ነገር ግን የመጨረሻውን ውሳኔና ማጣራት ለአእምሮአችን እንተው!
በንቃት እንጠቀም፣ በዕውቀት እንመራ!